ቀጥታ፡

የቴክኖሎጂ ፓርኩ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ግንባታ ያለው ሚና እንዲያድግ በትኩረት ይሰራል-በለጠ ሞላ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 21/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ በሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ ያለው ሚና እንዲያድግ በትኩረት እንደሚሰራ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆነውን የቴክኖሎጂ ፓርክ የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

አመራሮቹ የፓወር፣የኢንተርኔት፣ የውሃና መሰል መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ተቋማት መካከል “IE Networks” ፣ “RedCloud” ፣ “MK Digital Security Solutions PLC” ፣ “Uminers Datacenter” እና “XDMT Datacenter” ተመልክተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ፓርኩ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ሚናውን ለመወጣት የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ተቋማትን በውስጡ እያደራጀ ነው ብለዋል።

በፓርኩ ከዚህ በፊት ይነሱ የነበሩ የመሰረት ልማትና ምቹ የስራ ከባቢ አለመሟላት ችግሮች በመፍታት የግል ዘርፍ የቴክኖሎጂ ተቋማትን ጥያቄ ለመመለስ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

ፓርኩ የዕውቀት ሽግግር ማዕከል ሆኖ እንዲወጣ በትኩረት መሰራት እንዳለበትም የገለጹት ሚኒስትሩ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ራዕይ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም