የቡና ምርት ሰንሰለት ገቢራዊ የተደረጉ ሪፎርሞች ውጤት አስገኝተዋል-ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ምርት ሰንሰለት ገቢራዊ የተደረጉ ሪፎርሞች ውጤት አስገኝተዋል-ባለስልጣኑ
አዳማ፤ ታኅሣሥ 21/2017 (ኢዜአ)፡- የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ በቡና ምርት ሰንሰለት ገቢራዊ የተደረጉ ሪፎርሞች ውጤታማ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የቡና ምርት ትመና እና የቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመም ልማት ፓኬጅ ሠነድ ምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ እንደገለፁት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የቡና ምርታማነት ለመጨመር በተከናወኑ የሪፎርምና የንቅናቄ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።
ከቡና ምርት አሰባሰብና ገበያ ድረስ ባለው ሂደት ላይ በተከናወኑ ተግባራት በኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
"በአርሶ አደሩ፣ በባለሙያውና በአመራሩ ዘንድ የነበረውን የአመለካከትና የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት የቡና ምርታማነት ላይ ለውጥ አምጥተናል" ሲሉም አክለዋል።
አማካይ የቡና ምርታማነትን በሄክታር ወደ ስምንት ነጥብ አምስት በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በኦሮሚያ ንግድ ቢሮ የቡና ግብይት ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ በንቲ በበኩላቸው፤ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እስከ ግብይት ድረስ በተሰራው ስራ የቡና ምርታማነት መሻሻሉን ተናግረዋል ።
በክልሉ በቡና ዛፍ ጉንደላና በነቅሎ ተከላ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፤ በክልሉ ምርታማነቱን በአማካኝ በሄክታር ከሰባት ነጥብ አምስት ኩንታል ወደ ዘጠኝ ኩንታል ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ እንደገለፁት፤ በጫካ፣ በከፊል ጫካ፣ በጓሮና በዘመናዊ ቡና ልማት ላይ በክልሉ የተሻለ ስራ ተሰርቷል።
"በተለይ በተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም፣ በአረም ቁጥጥርና ኩትኳቶ ላይ በመስራታችን በምርታማነት የተሻለ ውጤት አግኝተናል" ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ቡናና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቀሬ በበኩላቸው፤ በክልሉ በቡና ምርትና ምርታማነት ላይ በተሰራ ስራ የተሻለ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
በተለይ በግብይትና ምርት አሰባሰብ አመራሩ፣ ባለሙያውና አርሶ አደሩ "በቅንጅት የዘርፉን ሪፎርም ውጤታማ በማድረጋቸው የተሻለ ውጤት አግኝተናል " ሲሉ አክለዋል።
See insights
Boost a post
Like
Comment
Send
Share

