ቀጥታ፡

መንግሥት የሀገርን ገጽታ የሚያጎሉ ጠንካራ የሚዲያ ተቋማት እንዲፈጠሩ ይደግፋል

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 21/2017(ኢዜአ)፦ መንግሥት የኢትዮጵያን ገፅታ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው የሚያሳዩ ጠንካራ የሚዲያ ተቋማት እንዲኖሩ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ያስገነባውን ዘመናዊ ስቱዲዮ ጎብኝተዋል።


 

አሚኮ ቀድሞም የተሻለ የሚዲያ መሠረተ ልማት እንደነበረው በማውሳት፥ በአዲስ አበባ የገነባው ስቱዲዮ ደግሞ ዘመኑን የዋጀ የሚዲያ ቴክኖሎጂን ያሟላ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

ሚዲያ ለህዝብ ድምፅ፣ ለመንግሥት ፖሊሲ መሳካትና ለሀገር ግንባታ ወሳኝ አቅም እንዳለው በመጥቀስ፥ አሚኮም ባለፉት ዓመታት ለህብረተሰብ ለውጥ የሚጨበጥ አበርክቶ ነበረው ብለዋል።

በአዲስ አበባ የገነባቸው ዘመናዊ ስቱዲዮዎች ተልዕኮውን ለማሳካት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑትም ገልጸዋል።

ዘመኑ ግለሰብ ዘመናዊ ስልኮችን በመጠቀም መረጃን ያለ ገደብ የሚያሰራጭበት መሆኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህንን የተረዳ የሚዲያ አሠራር ወሳኝ ነው ብለዋል።

ለዚህም ከተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታና እያደገ ከመጣው ቴክኖሎጂ ጋር የሚራመድ አሰራር፣ የሀሳብና የይዘት አቅም እንዲሁም የሰው ኃይል ግንባታ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሁሉም ዜጋና የመንግሥት አመራር መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ገንቢ መልዕክቶችን በማስተላለፍ የአጀንዳ የበላይነትን መያዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፌደራል መንግሥት ኢትዮጵያ የሚዲያ የበላይነትን በመያዝ በዓለም ስራዎቿን እንድትገልጥ አሚኮን ጨምሮ ለጠንካራ የሚዲያ ተቋማት ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው አሚኮ ከቴክኖሎጂ ባለፈ፣ በአመለካከት፣ በብቃትና በውጤታማነት የሚሠሩ የሚዲያ ሙያተኞችን እያፈራ ነው ብለዋል።

ለህብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን የሚለውን መለያውን በተግባር በመግለጥ ለአማራ ህዝብንና ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ ከአጎራባች ሀገራት ጋር የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከርና ገዥ ትርክትን በመገንባት ዋነኛ መሳሪያ በመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የአሚኮ ቦርድ ሰብሳቢ ይርጋ ሲሳይ፥ አሚኮ በክልሉ የልማትና የሰላም ሥራዎችን ለማሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለውን ብዝሃነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ በተለያዩሮ እንዲቀጥል ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም