በክላስተሩ ዘላቂና አስተማማኝ የመድሀኒት አቅርቦት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሪፎርም እየተደረገ ነው- አገልግሎቱ

ሀዋሳ፤ ታኅሣሥ 21/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክላስተር ለጤና ተቋማት ዘላቂና አስተማማኝ የመድሀኒት አቅርቦት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሪፎርም እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለፀ።

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የደቡብ ኢትዮጵያ ክላስተር አስተባባሪና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሰ ተቋሙ በሚያከናውናቸው የሪፎርም ሥራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ተቋሙ ለህብረተሰቡ የሚያስፈልጉ መድኃኒቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከመንግስት ተቋማት ጋር የዱቤ ሽያጭ ውል በመግባት ሲያቀርብ ቢቆይም እስካሁን ያልተከፈለ ከፍተኛ ተሰብሳቢ ገንዘብ እንዳለ ጠቁመዋል።

ለአብነትም በክላስተሩ ሥር ባሉ የሀዋሳ፣ አርባ ምንጭና ነገሌ ቦረና ቅርንጫፎች ከ199 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንዳልተከፈለው ጠቅሰዋል።

በዚህም አገልግሎቱን በአዲስ መልክ ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሰረት ለጤና ተቋማቱ የክፍያ ችግሮችን በመቅረፍ ዘላቂና አስተማማኝ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የአሰራር ለውጦች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

በዚህም ከመድኃኒት አቅርቦት አኳያ ስርዓቱ የጤና ተቋማት ዓመታዊ የመድኃኒት ፍላጎታቸውን ተንብየውና መጥነው እና በበጀት አስደግፈው ውል የሚገቡበት አሰራር እንደሚዘረጋ አስረድተዋል።

አዲሱ አሰራር በዱቤ የወሰዱትን መድኃኒት ክፍያ በወቅቱ ያልከፈሉ ጤና ተቋማት ክፍያቸውን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲከፍሉ ያደርጋል ብለዋል።

በግማሽ ዓመት ውስጥ ካልከፈሉ ደግሞ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በባንክ ውስጥ ካላቸው ሒሳብ ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ለአገልግሎቱ ገቢ እንዲደረግ የሚያስገድድ መሆኑንም አስረድተዋል።

ተቋማት ከዚህ ቀደም በዱቤ ለወሰዱት መድሀኒት ክፍያ እስካልከፈሉ ድረስ ሌላ የመድኃኒት አቅርቦት እንደማያገኙ በለውጥ አሰራሮች ውስጥ መካተቱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም