ቀጥታ፡

ባንኩ ከውጭ ከሚገቡ ባንኮች ጋር ለመወዳደር የሚያስችል አቅም ገንብቷል- አቶ አቤ ሳኖ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 21/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፒታል አቅሙና ዓለም አቀፋዊ የባንክ አሰራር ስርዓት በመተግበሩ ከውጭ ከሚገቡ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርገው አቅም መገንባቱን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።

የውጭ ባንኮች በሀገር ውስጥ ባንክ አገልግሎት ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው የባንክ ሥራ አዋጅ በቅርቡ መፅደቁ ይታወቃል።

አዋጁ የውጭ ባንኮችና ኢንቨስተሮች እንዲገቡ መፍቀዱም ቀጣይነት ያለው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ለማስመዝገብ እንደሚያስችል ተገልጿል።

በተለይም የፋይናንስ እና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ለማሳደግ፣ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር፤ ዓለም አቀፍ ትስስር፣ ተወዳዳሪነትና ውጤታማነት ለመጨመር ያስችላል።

አዋጁን ተከትሎ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ የውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገልጿል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባንኩ ከግዙፍ የውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር የካፒታል አቅሙን የማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙንና የአሰራር ሥርዓቱን ደግሞ የማዘመንና ውጤታማ የማድረግ ሥራ ትኩረት ተደርጓል።

የባንኩን ካፒታል በተመለከተ፤ ባንኩ ቀደም ሲል በተለይም ለግዙፍ ፕሮጀክቶች ያበደራቸው ብድሮች በወቅቱ አለመመለሳቸውን ተከትሎ የባንኩ የፋይናንስ ሁኔታ (balance sheet) መበላሸቱን ጠቅሰው ይህንን የማስተካከል ሥራ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ለዚህም መንግሥት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል ለማስተካከል የ900 ቢሊየን ብር ቦንድ እንዲያገኝ መደረጉ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የባንኩን ካፒታል ከነበረበት መጠን ከእጥፍ በላይ ማሳደጉን ነው ያስረዱት።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ባንኩ ከዓለም ባንክ የ650 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደሚጠብቅ ጠቅሰው ይህም የባንኩን ካፒታል በማስተካከልና አቅሙን በማጎልበት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ሌላው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከውጭ ባንኮች ጋር እኩል እንዲራመድና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለውን የቴክኖሎጂ አሰራር በተለይም ጠንካራና ውጤታማ የዲጂታል መሰረተ ልማቶች ከወዲሁ ሥራ ላይ ማዋሉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም የጥሬ ገንዘብ እጥረት ያጋጥመው እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ ሥራ ላይ በዋለው ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት ባንኩ የጥሬ ገንዘብ ችግር ላጋጣቸው ባንኮች ጭምር መድህን መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የብድር አስተዳደር ሥርዓቱን የማስተካከል ሥራ መሰራቱን ጠቅሰው በዚህም አመርቂ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም ባንኩ ያሉትን ቅርንጫፎች ውጤታማና ትርፋማ እንዲሆኑ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ እየተደራጁ መሆኑን ጠቅሰው በቅርብ ርቀት ላይ ያሉ ቅርንጫፎችን የማወሃድ ሥራም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል ማሳደግ ጨምሮ የአሰራርና ሥርዓትን ላይ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች ባንኩ ከውጭ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያስችለው አቶ አቤ ሳኖ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም