ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዋንጫ ተጨማሪ አምስት ክለቦች ወደ ሶስተኛ ዙር ተሸጋግረዋል 

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 21/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል።

የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 0 አሸንፏል።

አጥቂዎቹ ቢኒያም ጌታቸው እና አዲስ ግደይ የማሸነፊያዋን ግቦቹን አስቆጥረዋል።

በሌላኛው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ስልጤ ወራቤን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።


 

ሙጂብ ቃሲም ሶስት ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ሀትሪክ ሲሰራ ወንድወሰን በለጠ ቀሪዎቹን ሁለት ግቦች ለባህር ዳር ከተማ አስቆጥሯል።

ሀዲያ ሆሳዕና ሰመረ ሀፍታይ፣ ኢዮብ አለማየሁ እና ብሩክ በየነ በጨዋታ እንዲሁም ከድር ኩሊባሊ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠሯቸው ጎሎች ጋሞ ጨንቻን 4 ለ 0 ረቷል።

በሌላኛው መርሃ ግብር ሃላባ ከተማ ደደቢትን 2 ለ 1 አሸንፏል። ዮሐንስ ዘገየ በራሱ ላይ እና ፋሲል አበባየሁ ለሃላባ ከተማ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

አሸናፊ ተስፋዬ ለደደቢት ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል።

በተጨማሪም ሐረር ከተማ አምቦ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል። እሸቱ ጌታሁን እና ሃቢብ ሳቢት የግቦቹ ባለቤት ናቸው። 


 

የዛሬ ጨዋታዎችን ተከትሎ የኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር ተጠናቋል። 
በአጠቃላይ 16 ክለቦች ወደ ሶስተኛው ዙር አልፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ከታህሳስ 18 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እና በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ተከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ኢትዮጵያን ወክሎ በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይሳተፋል።

በ1937 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ 80 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም