የእንስሳት ምርታማነት ዕድገትን ለማስቀጠል ለተመጣጠነ መኖ አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቷል- ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳት ምርታማነት ዕድገትን ለማስቀጠል ለተመጣጠነ መኖ አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቷል- ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ ፤ ታኅሣሥ 21/2017(ኢዜአ)፡- የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ አቅርቦትን ተደራሽ በማድረግ የዘርፉን ምርታማነት ለማስቀጠል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
ዘጠኝ የተመጣጠነ መኖ አምራች ባለሃብቶች ከዘጠኝ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ተኪ ምርቶችን በሃገር ውስጥ ለማምረት የተያዘውን ግብ ከማሳካት በተጨማሪ የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም የሚያጎለብት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፉን በፊት ከነበረበት አሁን ላይ ምርታማ እንዲሆን አስችሎታል።
አያይዘውም በተያዘው በጀት ዓመት 150 ሚሊዮን የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት ለማሰራጨት ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዘርፉን ምርታማነት ዕድገት ታሳቢ ያደረገ የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ አቅርቦት እንዲኖር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የመኖ ማምረቻ ማሽነሪዎችን የሚያመርቱ አምራቾች እንዲሁም የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ የሚያመርቱ አምራች ባለሃብቶች በሚፈለገው ልክ እና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲያመርቱ አሳስበዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሃመድ የመኖ ማቀነባበሪያና ሌሎች የግብርና ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ ማሽነሪ አምራች እንዱስትሪዎች ለማምረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።