ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተሰጠው ትኩረት ምርቶቻቸውን በጥራት በማምረት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስችሏል - የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት - ኢዜአ አማርኛ
ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተሰጠው ትኩረት ምርቶቻቸውን በጥራት በማምረት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስችሏል - የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 21/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት የለውጥ አመታት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተሰጠው ትኩረት ምርቶቻቸውን በጥራት በማምረት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻሉን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር)ገለፁ።
ከታህሳስ 21 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ "የኛ ምርት፣ ለእኛ" የአምራች ኢንተርፕራይዞች ባዛር በአዲስ አበባ ተከፍቷል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ አመታት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶል፡፡
በመሆኑም መንግስት የስራ ፈጣሪዎች እንዲበረታቱና እንዲያድጉ ለማድረግ ለኢንተርፕራይዞች የተለያየ አቅም የመፍጠርና ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢንተርፕራይዞችን ቁጥር በመጨመር፣ የማምረት አቅምን በማሻሻል፣ ተኪ ምርትንና ኤክስፖርትን በማስፋፋት፤ የገበያ ትስስርን በማስፋት ላይ ሰፊ ስራ መሰራቱንም አመላክተዋል፡፡
በዚህም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አምራች ኢንተርፕራይዞች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን ተከትሎ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን በጥራት በማምረት የተወዳዳሪነት አቅማቸው እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት።
የአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ውጤታማ ሆኖ እንዲመራም ከመንግስት የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ሀገር አቀፍ የአምራች ኢንተርፕራይዝ ባዛርም ኢንተርፕራይዞች በምርት ትውውቅና ሽያጭ እንዲሁም የእርስ በእርስ ተሞክሮን ልውውጥና ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል ።
በባዛሩ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ 70 የሚሆኑ አምራቾች በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያ፣ በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች፣ በእንጨትና ብረታ ብረት የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተመላክቷል።