ከጂቡቲ ፕሬዝዳንት ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ከጂቡቲ ፕሬዝዳንት ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ ታኅሣሥ 21/2017(ኢዜአ)፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር በወደብ አጠቃቀምና በሌሎች የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናገሩ።
በጅቡቲ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ሚኒስትሩ ከጂቡቲ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት የጉብኝቱ ዓላማ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ምክክር ለማድረግ ነው።
ኢትዮጵያና ጂቡቲ በጣም ልዩ እና ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ከውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማህሙድ አሊ የሱፍ ጋር በሁለትዮሽ እና በቀጣናዊ የፖለቲካና የደህንነት ጉዳዮች በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በንግድ ጉዳዮች፣ በወደብ አጠቃቀም እና በወቅታዊ ቀጣናዊ ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ከባለስልጣናቱ ጋር ገንቢ እና ፍሬያማ ውይይት እንዳደረጉ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያና ጂቡቲ በባቡር፣ በወደብና የመሰረተ ልማት መስኮች ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው።
የኢትዮጵያ እና ጂቡቲ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እ.አ.አ በ1984 እንደተጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ።