ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የትይዩ ገበያውን ማዳከምና የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ማሳደግ አስችሏል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2017(ኢዜአ)፡- የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የትይዩ ገበያውን አቅም በማዳከም እና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ፡፡

ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ለመተግበር፣ ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ተመንን በገበያ እንዲመራ ለማስቻል ብሔራዊ ባንክ ሀምሌ 2016 ዓ.ም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ተግባራዊ መድረጉን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ከፍተኛ ተመራማሪ አቡሌ መሀሪ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት በትይዩ እና በመደበኛው ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ልዩነት 103 በመቶ በላይ ነበር፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የብር ዋጋ በገበያ እንዲወሰን በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ልዩነቱን ማጥበብ ተችሏል ብለዋል፡፡

በዚህም በመንግሥት ብርቱ ጥረት እና ተጨማሪ ብድር በመገኘቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሊያደርሰው ይችላል ተብሎ የተሰጋው የዋጋ ንረት የጎላ ጫና ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የባንክና ፋይናንስ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ተወልደ ግርማ(ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

የካፒታል ማርኬት መጀመር፣ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያስችለው የባንክ ስራ አዋጅ መጽደቅ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ጉልህ ለውጦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሬሚታንስ እና በሌሎች ዘርፎች በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ መጠን እድገት አሳይቷል ብለዋል፡፡

ሪፎርሙ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ከፍተኛ ተመራማሪ ናስር የኑስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ከሀምሌ 2016 እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም በተደረገው ጥናት በትይዩ እና መደበኛው ገበያ መካከል ያለው ልዩነት በእጅጉ ቀንሷል ብለዋል፡፡

እነዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የታለመለትን ግብ እየመታ መሆኑን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም