ቀጥታ፡

ተቋማት ከሙስና እና ብልሹ አሰራር የፀዱ ከሆነ የተልዕኮ አፈፃፀማቸው ስኬታማ ይሆናል - የሠላም ሚኒስትር መሀመድ ኢድሪስ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2017(ኢዜአ)፡- ተቋማት ከሙስና እና ብልሹ አሰራር የፀዱ ከሆነ የተልዕኮ አፈፃፀማቸው ስኬታማ ይሆናል ሲሉ የሠላም ሚኒስትር መሀመድ ኢድሪስ ገለጹ።

ለሠላም ዘርፍ አመራሮች "ሥነምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት" በሚል መሪ ሀሳብ ዘርፍ ተኮር የሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።


 

በስልጠና መድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር መሀመድ ኢድሪስ ተቋማት ከሙስና እና ብልሹ አሰራር የፀዱ ከሆነ የተልዕኮ አፈፃፀማቸው ስኬታማ ይሆናል ብለዋል።

በሀገራችን የተለያዩ ግጭቶች ከሚነሱባቸው ምክንያቶች መካከል የመልካም አስተዳደር እና ብልሹ አሰራር ችግር ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተቋማችን አመራርና ሠራተኛ በሥነምግባሩ አርዓያ በመሆንና የሥራ ሰዓትን ለተፈለገው ዓላማ በአግባቡ በመጠቀም ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መከላከል ያስፈልጋል ማለታቸው ተገልጿል።

ስልጠናው ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እንደሚያግዝ ገልፀው፥ ግንዛቤ ከመፍጠሩ ባሻገር በችግር ፈጣሪ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሉ የሥነምግባር መከታተያ ክፍል አመራርና ባለሙያዎች በየጊዜው የሙስና ተጋላጭነት ጥናት በማካሄድ ብልሹ አሰራር የሚስተዋልባቸውን ክፍሎች በመለየት ቀዳዳውን መድፈን ያስፈልጋል ማለታቸውም እንዲሁ።


 

የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፈቃዱ ሰቦቃ በበኩላቸው ስልጠናው በሥነምግባሩ አርዓያ የሆነ አመራር ከማፋራት ባሻገር የፀረ-ሙስና ትግሉን አጋዥ የሚሆን አመራርና ሠራተኛ ለማፍራት ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም ሁለቱ ተቋማት ተልዕኳቸውን መወጣት የሚችሉት ለኅብረተሰቡ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስልጠና በመስጠት መሆኑን አመላክተዋል።

የተቋማት አመራሮች ደካማ መሆን የሙስና እና ብልሹ አሰራር መበራከት ምክንያት መሆኑን ገልፀው፥ አመራሩ ከብልሹ አሰራር ነፃ በመሆን ለህዝብ የሚጠበቅበትን አገልግሎት መስጠት አለበት ማለታቸውም የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም