የኮሪያ ሪፐብሊኩ የመድኃኒት አምራች ድርጅት በኢትዮጵያ ፋብሪካ በመክፈት የአፍሪካ ገበያ ተደራሽነቱን ማስፋት እንደሚፈልግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪያ ሪፐብሊኩ የመድኃኒት አምራች ድርጅት በኢትዮጵያ ፋብሪካ በመክፈት የአፍሪካ ገበያ ተደራሽነቱን ማስፋት እንደሚፈልግ ገለጸ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 21/2017(ኢዜአ)፡- ዎንኪሶ(Wonkiso) የተሰኘው የኮሪያ ሪፐብሊክ የመድኃኒት አምራች ድርጅት በኢትዮጵያ ፋብሪካ በማቋቋም የአፍሪካ ገበያ ተደራሽነቱን ማስፋት እንደሚፈልግ አስታወቀ።
በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከድርጅቱ ኃላፊ ጁንግ ቼኦል ሊ ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ደሴ ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ወሳኝ የሆኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገች እንደምትገኝና ይህም ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዳደረጋት ገልጸዋል።
የድርጅቱ ተወካዮች ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንዲያደርጉም አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ጋብዘዋል።
የዎንኪሶ(Wonkiso) ድርጅት ኃላፊ ጁንግ ቼኦል ሊ ድርጅታቸው በኮሪያ ሪፐብሊክ ውስጥ ወደ አምስት ሺህ ለሚደርሱ የመድኃኒት መሸጫ መደብሮች ምርቱን እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በኢትዮጵያ የመድኃኒት ማምረቻ ፋብሪካ በማቋቋም በአፍሪካ ገበያ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ለማስፋት ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን በሴኡል የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።