በክልሉ የተጀመሩ የግብርና ኢንሼቲቮችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተጀመሩ የግብርና ኢንሼቲቮችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2017(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተጀመሩ የግብርና ኢኒሼቲቮችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።
ባለፉስ ሶስት ዓመታት በክልሉ የሚገኙ አርሶ-አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚረዳ አዲስ የግብርና ኢንሼቲቭ በመቅረጽ ተግባራዊ መደረጉ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አስተዋጽኦው ወሳኝ መሆኑንም አመልክቷል።
በክልሉ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ እንዲሁም በቡና ልማት ዘርፍ አርሶ አደሩ ያስመዘገበው እመርታ ለሌሎችም ክልሎች ተሞክሮ መሆን የሚችል መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው መግለጹም ተጠቁሟል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የመሬት ለምነትን ለመጠበቅ የተከናወነው ስራ አበረታች መሆኑን መግለጹን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በክልሉ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት መኖር፣ የእንስሳት በሽታ ክትባት እጥረት፣ የቅመማቅመም ህግ ክፍተቶች መኖር፣ ለአርሶ አደሮች የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት እና የገበያ ትስስር ክፍታት መኖር ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ መሆናቸውንም አሳስቧል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አህመድ ሀቢብ በበኩላቸው፤ ቋሚ ኮሚቴው የሰጠውን ግብረ መልስ ግብዓት በመሆኑ የበለጠ እንድንሰራ ያግዛል ብለዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ያስቀመጣቸውን በማስፋት እንዲሁም እንደ ክፍተት የጠቀሳቸውን ጉዳዮች በማረም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ድህነትን ለማሸነፍ የተጀመረውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ መግለጻቸውም ተመላክቷል።