ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ አምስት ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል።

ሐረር ከተማ ከአምቦ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ባህር ዳር ከተማ ከስልጤ ወራቤ ከቀኑ 7 ሰዓት፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በተመሳሳይ ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ይደረጋሉ።

ሃላባ ከተማ ከደደቢት ከቀኑ 7 ሰዓት እንዲሁም ጋሞ ጨንቻ ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ይጫወታሉ።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች የአምናው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ኢትዮጵያ ቡና በስሑል ሽሬ 2 ለ 1 ተሸንፎ ከውድድሩ ተሰናብቷል።

በሌሎች መርሃ ግብሮች መቻል አዲስ አበባ ከተማን እንዲሁም ነገሌ አርሲ ደሴ ከተማን በተመሳሳይ 4 ለ 0 እንዲሁም ቦዲቲ ከተማ አዳማ ከተማን እና ሲዳማ ቡና ሶሎዳ አድዋን በመለያ ምት በማሸነፍ ወደ ሶስተኛው ዙር አልፈዋል።

እስከ አሁን 11 ክለቦች ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፉ ሲሆን የአምናው የፍጻሜ ተፋላሚ ወላይታ ድቻ፣ መቻል፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ሃዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ካለፉት ክለቦች መካከል ይገኙበታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ፣ አርባ ምንጭ ከተማ እና መቀሌ 70 እንደርታ በሁለተኛው ዙር ከተሰናበቱት ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ኢትዮጵያን ወክሎ በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይሳተፋል።

በ1937 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ 80 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም