የውጭ አገራት ጎብኚዎች በመዲናዋ ለውጥና በቱሪዝም መስህቦቿ መደነቃቸውን ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ አገራት ጎብኚዎች በመዲናዋ ለውጥና በቱሪዝም መስህቦቿ መደነቃቸውን ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 21/2017(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ እየታየ ያለው ለውጥ ለቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው ሲሉ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ባላት ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ቅርሶች መደነቃቸውን ገልጸዋል።
ኡጋንዳዊው ቺንቱ ዮናስ በፈረንጆቹ የገና በዓል ሰሞን ወደ ኢትዮጵያን ከመጡ የውጭ አገራት ጎብኚዎች መካከል አንዱ ሲሆን በቆይታውም ጂንካን፣ ጎንደርንና አክሱምን ጨምሮ የተለያዩ ክልሎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ቺንቱ ቆይታውን አስመልክቶ አስተያየቱን ለኢዜአ አጋርቷል።
በአዲስ አበባ የተመለከተው የከተማ ልማት ጎብኚዎችን የሚስብና ለኢንቨስትመንት አመቺ ዕድል የሚፈጥር ነው ብሏል።
“እስካሁን ከጎበኘኋቸው ሁሉ ኢትዮጵያ አስደናቂ መዳረሻ ናት” ሲል ለኢትዮጵያ ያለውን አድናቆት ገልጿል።
ህንዳዊው አዴሌ አቭዛልሃን በበኩሉ በአዲስ አበባ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ መደነቁን ተናግሯል።
ሌላው ህንዳዊው ጎብኚ ጂሻን አሂሜድ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ላሳዩት እንግዳ ተቀባይነት አመስግኖ በኢትዮጵያ በተመለከተው ብዝሃ ባህል መደነቁን ገልጿል።
በመላ አገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎችም ለጎብኚዎችና ለኢንቨስትመንት የተመቹ መሆናቸውን ተናግሯል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ዘርፉ ለሀገር እድገት ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም የቱሪዝም መስህቦቿን በማስፋፋት፣ በመገንባትና ነባር መዳረሻዎችን ደግሞ በስፋት የማደስ ሥራ እየሰራች ትገኛለች።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢህ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመሩ እንደ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ያሉ ፕሮጀክቶች ሀገሪቱ የቱሪዝም አቅሟን ለመጠቀም ያላትን ቁርጠኝነት በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።