በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል

ጎንደር፤ታህሳስ 20/2017 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን በታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስልጣናት ቆሞስ አባ ዮሴፍ ደስታ በሰጡት መግለጫ፤ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ አግባብ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።
በዐሉን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ ለማክበር ዐብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለዚህም የጥምቀት በዓል የሚከናወንበትና ታቦታቱ የሚያርፉበትን የፋሲለደስ የባህረ ጥምቀት ስፍራ የጥገና ሥራ 95 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የበዓሉን ስፍራ ውበትና ጽዳቱ የሚያስጠብቁ እና በዓሉን ለመታደም የሚመጡ ምዕመናን፣ ሊቃውንት፣ ቀዳሾችንና አባቶችን እንዲሁም ሌሎች አንግዶችን ቦታ የሚያስይዙና ሰላሙን የሚያስጠብቁ ወጣቶች ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያዊ መሰረቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ መንፈሳዊ፣ ሃይማታዊና ባህላዊ ትውፊታዊ ስርዓት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ዝግጁቱም ይህንን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል።
መንግስት በኮሪደር ልማት በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የመስቀል አደባባይ የቀደመ ታሪክ ጠብቆ በማልማት ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ለማጎናጸፍ ያከናወናቸው ተግባራትንም አባ ዮሴፍ አመስግነዋል።
ጥምቀትን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችና ቱሪስቶች ከበዓሉ በተጨማሪ በጎንደር ከተማና አካባቢው የሚገኙ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል።