ብልፅግና ቃልን በተግባር እየፈጸመ ያለ ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ቃልን በተግባር እየፈጸመ ያለ ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2017(ኢዜአ)፡-ብልፅግና ቃልን በተግባር እየፈጸመ ያለ ህብረ-ብሔራዊ ፓርቲ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩና የሚነጣጥሉ ትርክቶችን ስብራት ለመጠገን ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
እንደ ሀገር የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ችግር ለህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ማጣት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አስታውሰው በዚህ ረገድ ብልፅግና መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የቆዩ ስብራቶችን በመጠገን አሰባሳቢና ገዥ ትርክቶችን በመፍጠር አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በ2023 ዓ.ም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ሰነቆ በሁሉም መስኮች እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ለበርካታ ዓመታት እየተንከባለሉ የመጡ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎች በሂደት ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ለአመታት ሲነሳ የነበረውን የክልልነት ጥያቄ ምላሽ መሰጠቱንና የተሰጠበት አግባብ በትልቅ ማሳያነት የሚወሰድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በኢኮኖሚ ዘርፍም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ የስንዴ ልማት፣ የመስኖ ስራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የቱሪዝም ማስፋፊያ፣ በኮሪደር ልማትና የህዳሴ ግድብ ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
እነዚህ ስኬቶች ብልፅግና ቃልን በተግባር እየፈጸመ ያለ ፓርቲ መሆኑን በተግባር የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡
የተጠቀሱትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተግባራት የተሳኩት በ2014 ዓ.ም በተካሔደው የብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተቀመጡ አገራዊ ራዕዮች ከተቀመጠላቸው ጊዜ ቀድመው እየተሳኩ መሆኑን ተከትሎ ህዝብ እና የአለም አቀፍ ተቋማት እውቅና እየሰጡ እንደሚገኙም አንስተዋል፡፡
ከኢኮኖሚው ዘርፍ በተጨማሪ በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲው ዘርፍም ተመሳሳይ ስኬቶች መመዝገባቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎችም አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙም አንስተዋል፡፡