ቀጥታ፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት አዙሯል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2017(ኢዜአ)፡- በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የታጠቁ ቡድኖች የሰላም አማራጭን በመከተላቸው የተፈጠረው አስተማማኝ መረጋጋት ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር አስችሏል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰፊ የኢንቨስትመንት ፍሰት፣ የማዕድናት፣ የእርሻ መሬትና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገኛ መሆኑ ለሀገር ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።

ይህም የሀገርን ብልፅግና ለማሳካት ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ አበርክቶ ቢኖረውም፥ የሀገር እና የክልሉ ልማት እንዳይሳካ የሚፈልጉ አካላት ግጭት በማስነሳት ለማደናቀፍ መሞከራቸውን አውስተዋል።

የክልሉና የፌደራል መንግሥታት የታጠቁ ቡድኖችን ፖለቲካዊ ፍላጎት በማጤን በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት ሰፊ ርቀት መጓዛቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም በሀገር ውስጥና በአጎራባች አካባቢዎች ሆነው ክልሉን ሲያተራምሱ ከነበሩ አካላት ጋር በመወያየት የሰላም ስምምነት መፈጸሙን አንስተዋል።

ሁሉም የታጠቁ ቡድኖች በሚባል ደረጃ ትጥቃቸውን አስረክበው በተሃድሶ ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን ነው የገለጹት።

በዚህም በክልሉ አስተማማኝ ሰላም መፈጠሩን ጠቅሰው የልማት ስራዎችና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ መነቃቃት አሳይተዋል ነው ያሉት።

በመሆኑም በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ሰላም በመምጣት ለሀገር ሰላምና ልማት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቀጣይነት ህብረተሰቡን ያሳተፈ አወንታዊ ሰላም ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አንስተዋል።

መንግሥት ሰላምን ለማፅናት ከእሳት ማጥፋት ይልቅ ለዘላቂ መፍትሔዎች ትኩረት መስጠቱን ገልጸው፥ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችም ለሰላም የተደረገላቸውን ጥሪ ሊቀበሉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም