የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከጂቡቲ አቻቸው ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከጂቡቲ አቻቸው ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2017(ኢዜአ)፡- በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ከጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃሙድ አሊ የሱፍ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳይ ላይ ተወያይቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) በሁለቱ ወንድማማች ሀገራት መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለጎረቤት ሀገራት ትስስር እንደምሳሌ የሚነሳ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በመጥቀስ፣ አሁንም አልሸባብን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኛነት ገልጸዋል።
ልዑኩ በጂቡቲ የሚሰጠውን የወደብ አገልግሎት ይበልጥ ለማቀላጠፍ፣ የነዳጅ ተርሚናል አቅም ለመጨመር፣ የዲኪል-ጋላፊ መንገድ ግንባታ የማጠናቀቅ ሂደት፣ የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች እና አጠቃላይ የገቢ-ወጪ ምርት ዝውውር ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጂቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃሙድ አሊ የሱፍ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ወዳጅነት በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ቤተሰባዊነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመግለጽ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ጂቡቲ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን ላይ እየሰራች ያለችውን ስራ በማመስገን፣ አልሸባብን መከላከል ላይ በጋራ እንደምትሰራ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን የነዳጅ ፍላጎት ባማከለ መልኩ የነዳጅ መስመር ከደመርጆግ ወደብ ጋር ለመያያዝ ተጨማሪ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የዲኪል-ጋላፊ የመንገድ ስራም በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውም ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።