በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉ የቆዩ ችግሮች ሁነኛና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ የሚቻለው በምክክር ብቻ ነው - ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉ የቆዩ ችግሮች ሁነኛና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ የሚቻለው በምክክር ብቻ ነው - ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉ የቆዩ ችግሮች ሁነኛና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ የሚቻለው በምክክር ብቻ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ በመሻት ብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር በአዋጅ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡
ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 በይፋ ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባ ሲሆን ከቅድመ ዝግጅት ስራዎች ጀምሮ አሁን ላይ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
አጠቃላይ የኮሚኝኑን የስራ እንቅስቃሴና የምክክር ሂደቱን በማስመልከት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው ለኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮች ሁነኛና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ የሚቻለው በምክክር ብቻ መሆኑን በማንሳት የኮሚሽኑም ስራ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን በስኬት ቀጥሎ አሁን ላይ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በእስካሁን ሂደቱ ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉንም አካታች ባደረገ መልኩ ምክክሩ በአሳታፊነቱ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተሳታፊ ልየታ ባልተደረገባቸው ቀሪ አካባቢዎች ስራ መጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አንስተው ከአጋዥ አካላት ጋር ትብብሩን በማጠናከር በስኬት ለመቀጠል ኮሚሽኑ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።