የኮሪደር ልማቱ ለብስክሌት ስፖርት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ስፖርቱን የሚቀላቀሉ ታዳጊዎች እየተበራከቱ መጥተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱ ለብስክሌት ስፖርት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ስፖርቱን የሚቀላቀሉ ታዳጊዎች እየተበራከቱ መጥተዋል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2017(ኢዜአ)፡- የኮሪደር ልማቱ ለብስክሌት ስፖርት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ስፖርቱን የሚቀላቀሉ ታዳጊዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በተጠናቀቁት የኮሪደር ልማቶች በታዳጊዎች በአዋቂዎች እና በቀድሞ ብስክሌተኞች መካከል የኮካ ኮላ ብስክሌት ሻምፒዮን ውድድር አካሂዷል፡፡
የብስክሌት ውድድሩ የተካሄደው ከቸርችል ጎዳና እስከ ለገሀር ባለው የኮሪደር መንገድ ላይ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን የበላይ ጠባቂ አቶ ረዘነ በየነ በከተማዋ የተከናወኑና የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከተማዋን ውብና ጽዱ ከማድረግ በተጨማሪ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲስፋፉ አግዘዋል፡፡
ግንባታዎቹ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እና ውድድሮችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠራቸው ባለፈ ህብረተሰቡ ስፖርትን እንዲያዘወትር አድርገዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የብስክሌት ስፖርት እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ሲሆን በተለይም ስፖርቱን የሚያዘወትሩ ታዳጊዎችን ቁጥር ከፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሲሳይ ተፈራ እንደገለጹት የኮሪደር ልማት አካል የሆነው የብስክሌት መንገድ ተወዳዳሪዎች ልምምዳቸውንና ውድድራቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፡፡
ውድድሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት በተጨማሪ የኮሪደር ልማቱ ለስፖርቱ ምን ያህል ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ የማስተዋወቅ አላማ ይዞ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የከተማዋ መንገዶች ለብስክሌት ምቹ አለመሆናቸውን ተከትሎ ለረጅም ቀናት ውድድር ሳያካሂዱ ይቆዩ እንደነበር የውድድሩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ የተሰሩ የብስክሌት መንገዶች ልምምዳቸውን ከአደጋ ስጋት ነፃ በሆነ መልኩ እንዲያከናውኑ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ለስፖርቱ አመቺ ሁኔታ በመፍጠሩ በተሻለ ሁኔታ በመዘጋጀት በውድድሩ እየተሳተፉ እንደሚገኙም ነው የገለጹት፡፡
የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ ህብረተሰቡ ብስክሌት የመጠቀም ባህሉ እያደገ መምጣቱን መታዘባቸውን ተወዳዳሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡