በትራንስፖርት ዘርፍ ተግባራዊ የተደረገው የአደረጃጀት ማሻሻያ የአገልግሎት አድማስን የሚያሰፋና ጥራትን የሚያሳድግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትራንስፖርት ዘርፍ ተግባራዊ የተደረገው የአደረጃጀት ማሻሻያ የአገልግሎት አድማስን የሚያሰፋና ጥራትን የሚያሳድግ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2017(ኢዜአ)፡- የትራንስፖርት ዘርፉን ተወዳዳሪ እና ሀገራዊ ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግ የተጀመረው የአደረጃጀት ማሻሻያ የአገልግሎት አድማስን የሚያሰፋና ጥራትን የሚያሳድግ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።
የዳበረ ኢኮኖሚ ለመገንባትና የምርቶችን ዝውውርና የገበያ ሰንሰለት ለማዘመን ጊዜውን የሚመጥን የማጓጓዣ ስርዓትና አደረጃጀት መፍጠር ይገባል።
በዚህ ረገድ የወደብ ልማት፣ የሎጂስቲክስ ማዕከላት፣ የባቡር፣ የአቪዬሽንና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን በዘመናዊ አደረጃጀት መምራት ያስፈልጋል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የትራንስፖርት ዘርፍን ይበልጥ ተወዳዳሪ እና ሀገራዊ ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግ አዲስ አደረጃጀት ተግባራዊ መደረጉን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም ከዚህ በፊት የህዝብና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው በማህበር በመደራጀት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይህንኑ ለማስተካከል ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ አደረጃጀታቸው ወደ ግል ንግድ፣ ወደ ሼር ካምፓኒ እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንዲለወጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በተካሄደው የአደረጃጀት ማሻሻያ የሰው ኃይል ቅጥርና ስምሪት፣ የቢሮ አደረጃጀት፣ የአሰራር ስርዓት አተገባበር እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
ማሻሻያው በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች የስራ አድማሳቸውንና ጥራታቸውን እንዲያሳድጉ እያገዛቸው መሆኑን ነው ያስታወቁት ፡፡
እንደዚሁም ከወረቀት የጸዳ አገልግሎት በዘንድሮ አመት በተሟላ መልኩ ለመተግበር እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተገናኘም የ3ኛ ወገን አሰራር ዲጂታላይዝድ መደረጉንም ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
የትራፊክ ቅጣት ክፍያና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶች በቀጣይ ዲጂታላይዝድ እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል መንገደኞች ባሉበት ሆነው ትኬት እንዲቆርጡ፣ የወንበር ቁጥራቸውን እንዲያወቁና ያለምንም እንግልት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚተገበረው ቴክኖሎጂ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ቴክኖሎጂው የሀገር አቋራጭ የስምሪት አሰጣጥን ቀልጣፋና ፍትሃዊ ከማድረጉ በላይ ሰው ሰራሽ የትራንስፖርት እጥረትን መከታተል የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እየለሙ የሚገኙ መተግበሪያዎች ወደ ስራ በሚገቡበት ወቅት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በማዘመን የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሻሻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡