የጥምቀትን በዓል በጎንደር ከተማ ለማክበር የዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል-ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀትን በዓል በጎንደር ከተማ ለማክበር የዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል-ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው

አዲስ አበባ፤ታህሣሥ 19//2017 (ኢዜአ)፦በዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል በልዩ ድምቀት በጎንደር ለማክበር የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የጥምቀት በዓል አከባባር አስመልክቶ ከከተማው የፀጥታ አካላት እና የማህበረሰብ የሰላም ዘብ ጠባቂ ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የማህበረሰብ የሰላም ዘብ ጠባቂዎች የጥምቀት በዓል በሰላምና በፍቅር በድምቀት ለማክበር ዝግጁ ነን ሲሉ ገልጸዋል።
ጥምቀት ለጎንደር ትልቅ በዓል ነው ይህን በዓል በሰላም ለማክበር ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
እንግዶችን በፍቅር እና ሰላማቸው ተጠብቆ በጎንደር ቆይታቸው ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች በጎንደር ጥምቀት እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንደገለጹት ሁሉም የሰላም ባለቤት በመሆን የጥምቀት በዓልን በሰላም ለማክበር መዘጋጀት ይገባል።
የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በልዩ ድምቀት እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም የማህበረሰብ የሰላም ዘብ ጠባቂዎች ወደ ስራ እንደሚገቡም አመልክተዋል።
በዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል በልዩ ድምቀት በጎንደር ለማክበር የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተስፋ መኮነን በበኩላቸው የማህበረሰብ ሰላም ዘብ ጠባቂ አካባቢውን ሰላም በማስከበር በኩል ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አሰፋ አሽቤ በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር የፀጥታ አካሉ አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
ለዚህ ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።