ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ጥቅምንያስቀደሙ ዘገባዎች ሊሰሩ ይገባል- ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 19/2017(ኢዜአ)፦ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ብሔራዊ ጥቅም ያስቀደሙ እና ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተከተሉ ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን "በግጭት አገናዛቢ እና በሰላም አዘጋገብ" ዙሪያ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ የሚዲያ ተቋማትን ከተቋቋሙለት ዓለማ አንጻር ግዴታቸውን እንዲወጡ የመከታተል፣ የመቆጣጠርና ፈቃድ የመስጠት ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው።

የስልጠናው ዓላማም የሚዲያ ባለሙያዎች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም፣ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በማስቀደም እንዲሰሩ ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ ምግባርን ባከበረ መልኩ ወጥ ኤዱቶሪያል ፖሊሲ ቀርጸው መመራት እንደሚገባቸው ገልፀው፤ በተለይም የሀገርና የህዝብ ጥቅምን ያስቀደሙ ይዘቶች ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በባለስልጣኑ የስትራቴጂክ ጉዳዮችና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሺወርቅ ግርማ፤ መገናኛ ብዙሃን የህዝብ አገልጋዮችና የመረጃ ምንጮች በመሆናቸው ተጨባጭ መረጃና የተሻለ ዕውቀትና ክህሎት በመያዝ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

ባለስልጣኑ ለተቋማቱ አስፈላጊውን ስልጠና እና ድጋፍ በመስጠት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮነ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች የሀገርና የህዝብ ወገንተኛ በመሆን ዕውነታን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊዘግቡ ይገባል ብለዋል።

የዓለምንና አጠቃላይ አህጉራዊውን ነባራዊ እውነታና አዝማሚያዎችን በአግባቡ በመረዳት በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስነ ምህዳር በጥልቀት በመረዳት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ዘገባ ማድረስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም