የአንካራው ስምምነት ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ባከበረ አግባብ የተደረገ ነው-የሕግ ባለሙያ - ኢዜአ አማርኛ
የአንካራው ስምምነት ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ባከበረ አግባብ የተደረገ ነው-የሕግ ባለሙያ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 19/2017(ኢዜአ)፦ የአንካራው ስምምነት ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ባከበረ አግባብ የተደረገ ስምምነት እንደሆነ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ ገለጹ።
በተርኪዬ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አቀራራቢነት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ተቀራርበው በመነጋገርና በመተማመን የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት አፅንተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕግ ምሁሩ ተዋናይ ሙላቱ፤ የአንካራው ስምምነት ለኢትዮጵያና ሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የላቀ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ስምምንት የተለያዩ አገራት መሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የደገፉት ታሪካዊ ሁነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የአንካራው ስምምነት ዓለም አቀፍ መርሆችን የተከተለና በሁሉም ረገድ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ተገቢነትና ህጋዊነት ያለው መሆኑን አንስተው ለቀጣናው የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ወሳኝ ድርሻ የሚኖረው መሆኑንም ተናግረዋል።
የአንካራው ስምምነት በቀጣናው የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የግጭትና አለመተማመን ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑንም አስረድተዋል።
በቀጣይ የሚደረጉ ቴክኒካል ስምምነቶችም በአገራቱ መካከል በሰጥቶ መቀበል መርህ ዓለም አቀፍ ህጎችን ባከበረ መልኩ እንደሚከናወን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።