የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 19/2017(ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሰረታዊ የኢኮኖሚ ለውጥ በማምጣት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል መሆኑን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር እና በጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና በይነ አፍሪካ ንግድ ጥናት ማዕከል በጋራ ያዘጋጁት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
መድረኩ በቀጣይ ጥር ወር በአዲስ አበባ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዶላር ዋጋ በገበያው መወሰኑ ያመጣው ጥቅም፣በሂደት ያጋጠሙ ችግር እና መፍትሔ ለማቅረብ የማጠናከሪያ ሃሳብ ማሰባሰቢያ ነው፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈሪ ጥያሩ፤ ኢትዮጵያ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ የፖሊሲ ለውጥ ማድረጓ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን አንስተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫዎት መሆኑን ጠቅሰው፥በአጭር ጊዜ ችግር ዘላቂ ጥቅምን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ የሚደረጉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ውይይቶችም ክፍተቶችን በመሙላት የማስተካከያ ርምጃዎች እንዲወሰዱ መክረ ሃሳብ ለማቅረብ ያግዛሉ ብለዋል፡፡
በመሆኑም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሰረታዊ የኢኮኖሚ ለውጥ በማምጣት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሚያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤የዶላር ዋጋ በገበያ እንዲተመን ከፍተኛ ምስቅልቅል ያጋጥማል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም በኢትዮጵያ ከታሰበውም በላይ የተረጋጋ ሁኔታ የታየበት ሆኗል ብለዋል፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በትይዩ መደበኛ ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ፣የባንኮችን የመሸጫና የመግዣ ዋጋ በማቀራረብ አዎንታዊ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
የህዝብን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ማረጋገጥ እንዲችል እንደ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ያሉ ተቋማት በጥናት ላይ የተመሰረተ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ እንዳለባቸውም አንስተዋል።
በጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና በይነ አፍሪካ ንግድ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ሰይፈ ታደለ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያውያን አብሮነትና በትብብር የመሥራት ባህል ለቀጣናዊ ትስስር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ውጤታማ ለማድረግ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ጠንካራ ተቋም መፍጠር እንደሚገባ ገልጸው፥ ሀብትን፣ ጉልበትና ገንዘብን በማቀናጀት ሥራ መፍጠር ይገባልም ነው ያሉት።