ስንዴ በዓመት ሶስት ጊዜ መመረቱ ምርትና ምርታማነትን ከመጨመሩ ባለፈ የሥራ ባህልን ቀይሯል - ኢዜአ አማርኛ
ስንዴ በዓመት ሶስት ጊዜ መመረቱ ምርትና ምርታማነትን ከመጨመሩ ባለፈ የሥራ ባህልን ቀይሯል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 19/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የበጋ ወቅትን ጨምሮ ስንዴን በዓመት ሶስት ጊዜ የማምረቱ ሂደት ምርትና ምርታማነትን ከመጨመሩ ባለፈ የሥራ ባህልን የቀየረ መሆኑን ግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ስንዴ በመኸር፣በበጋ እና በበልግ የማምረቱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በ2017 ዓ.ም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስከ አሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ሚኒስትር ዴኤታው ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ እስካሁን 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መታረሱን ገልጸው፥ 173 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ በሁሉም ክልሎች ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።
ባለፉት አምስት አመታት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኤኒሼቲቭ በተሰራው ሥራ ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን ከራሷ አልፋ ወደ ውጪ በመላክ የታሪክ እጥፋት ማስመዝገብ ችላለች ብለዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የበጋ ወቅትን ጨምሮ ስንዴን በዓመት ሶስት ጊዜ በማምረት ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ የሥራ ባህልን የቀየር መሆኑን ገልጸዋል።
የደረሱ የመኸር ሰብሎችን ከመሰብሰብ ጎን ለጎን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የበጋ መስኖ ስንዴ የማሳ ዝግጅት በማድረግ ስንዴን የመዝራቱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
የመኸር እርሻ ዘግይቶ በተዘራባቸውና ምርት ባልተሰበሰባቸው አካባቢዎችም በወቅቱ የበጋ መስኖ ስንዴ እርሻ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ከግብዓት አንጻረም ዘንድሮ የተሻሻሉ የስንዴ ዘር ለአርሶ አደሩ ቀድሞ መከፋፈሉን ገልጸዋል።
የአፈር ማዳበሪያም ቀድሞ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸው፥ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የውሃ አቅርቦትን በተመለከተ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችም ለአርሶ አደሩ መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።
ከበጋ መስኖ ስንዴ ጎን ለጎን የመደበኛ መስኖ፤የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች በልዩ ትኩረት እየተሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል።