ቀጥታ፡

ጋምቤላን ጨምሮ ትኩረት ሳያገኙ የቆዩ ብሔራዊ ፓርኮችን በመሰረተ ልማት ተደራሽ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ታልሟል

ጋምቤላ፤ ታኅሣሥ 19/2017(ኢዜአ)፦ ጋምቤላን ጨምሮ ትኩረት ሳያገኙ የቆዩ ብሔራዊ ፓርኮችን በመሰረተ ልማት ተደራሽ በማድረግ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ቅድሚያ ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፣ ባለስልጣኑ የብሔራዊ ፓርኮችን መሰረተ ልማት በማስፋፋት እንደ ሀገር በቱሪዝም ዘርፉ የታለመውን ለብዝሃ ኢኮኖሚ ትግበራ ዕውን መሆን በትኩረት እየሰራ ነው።

ብሔራዊ ፓርኮች ለቱሪዝም መስህብነት የሚውል ዕምቅ የተፈጥሮ ብዝሃ ህይወት ያላቸው ቢሆንም ቀደም ሲል ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ ሃብቱ በአግባቡ ለምቶ የሚፈለገውን ጥቅም ሳያስገኝ መቆየቱን ተናግረዋል።

በሰሜን ተራሮችና በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርኮች ከነበረው የተወሰነ እንቅስቃሴ ባለፈ ጋምቤላን ጨምሮ ሌሎች ብሔራዊ ፓርኮች ባለመልማታቸው የሚፈለገውን ጥቅም ሳያስገኙ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ቱሪዝም እንደ ሀገር ለብዝሃ ኢኮኖሚ ትግበራ ከተለዩ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በብሔራዊ ፓርኮች ያለውን ሰፊ ብዝሃ ህይወት በማልማት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለማዋል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በጨበራ ጩርጩራ፣ በባሌ ተራሮች፣ በአዋሽና በሌሎች ብሔራዊ ፓርኮች መዳረሻ እየተካሄዱ ያሉትን የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴዎች ለማሳያነት አንስተዋል።

በቅርቡም ከአፍሪካ ፓርኮች ጋር ስምምነት በማድረግ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች በስፋትም ሆነ በብዝሃ ህይወት ሃብቱ ቀዳሚ እንደሆነ የሚታወቀውን የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ወደ ልማት ለማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በባለስልጣኑና በክልሎች የሚተዳደሩና ከአጠቃላይ የሀገሪቱ መሬት የቆዳ ስፋት 10 ነጥብ 6 ከመቶ የሚሆነውን የሚይዙ፣ በዓለም የመረጃ ቋት የሚታወቁ 87 ፓርኮችና ጥብቅ ቦታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ ሃብቶች በአግባቡ ለምተው የሚፈለገውን ጥቅም እንዲያስገኙም መስሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር በመሆን በፓሊሲ፣ በህግ ማቀፎችና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም