የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ኃብት 1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር ደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ኃብት 1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር ደረሰ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 19/2017(ኢዜረአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ኃብት 1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም ባንኩን ተጋርጦበት ከነበረው የህልውና አደጋ ወደ ላቀ እድገት አሸጋግሮታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ በማብራሪያቸው ቀደም ሲል ባንኩ ይከተለው የነበረው የብድር አሰጣጥ ለከፍተኛ ችግር ዳርጎት መቆየቱን አስታውሰዋል።
በተለይም ለትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ቢሊዮን ብሮችን በዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ሲያበድር በመቆየቱ ባንኩ ላይ የህልውና አደጋ ጋርጦት እንደነበር አንስተው፥ አሁን በተደረጉ ማሻሻያዎች የላቀ ሽግግርና ስኬት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የባንኩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ምእራፍ ያሸጋገረ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁን ላይ በሁሉም ረገድ ጥሩ ቁመና ላይ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይም በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ጠንካራና ተወዳዳሪ በማድረግ ትርፋማነቱን ለማሳደግ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የባንኩ አጠቃላይ ኃብት አሁን ላይ 1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር እንዲሁም አጠቃላይ ቁጠባው 1 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር ደርሷል ነው ያሉት።
በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርአት ባንኩ ከውጭ ምንዛሬ ግኝት ባለፈ በቁጠባ ከፍተኛ እድገት እንዲያስመዘግብ እንዳስቻለው ተናግረዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ እስካሁን 217 ቢሊዮን ብር በቁጠባ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በለውጡ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመታገዝ ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያ የውጭ ባንኮች እንዲሳተፉ የሚፈቅደውን
የብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ አዋጅን ማጽደቁ ይታወሳል።
አዲሱ አዋጅ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግና ለምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ቀጣይነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል።