ለጋራ ዘላቂ ጥቅም ሲባል የባህር በር የማግኘት ጥረቱ የማይቀር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለጋራ ዘላቂ ጥቅም ሲባል የባህር በር የማግኘት ጥረቱ የማይቀር ነው
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 19/2017(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው ሀገራት ዘላቂ ጥቅም ሲባል የባህር በር የማግኘት ጥረቱ የማይቀር መሆኑን የታሪክ ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ ያደረጉት ስምምነት የቀጣናውን ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሴራ ያመከነ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ተናግረዋል።
የባህልና የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ ለኢዜአ እንዳሉት፥ ሁለቱ ሀገራት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት መስማማታቸው የሚደነቅና ለቀጣናው ሰላምና ልማት ወሳኝ ሚና ያለው ነው።
ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ቅድሚያ የሚሰጥ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዳላት ጠቅሰው፥ ስምምነቱ ለቀጣናዊ ትብብር መጠናከር ያላትን ጉልህ ሚና የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው ኢትዮጵያ የእውነትና የፍትሕ ሀገር መሆኗን አንስተው፥ ብሔራዊ ጥቅሟን የምታስከብረው የሌሎችን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ምስረታና ለተልዕኮዎች መሳካት ያበረከተችው አስተዋፅኦ በታሪክ ከፍ ብሎ የተቀመጠ መሆኑን አውስተዋል።
በተለይም ለቀጣናዊና አህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት የከፈለችው ዋጋ ማንም የማይተካው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እያደገ ያለውን የወጪና ገቢ ንግድ በአንድ ወደብ ብቻ ማሳለጥ ስለማትችል ብዙ ወደቦች እንደሚያስፈልጓት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ ተናግረዋል።
ሀገራዊ አቅሟን ማስተናገድ የሚያስችል የባህር በር ጥያቄ ማቅረቧ ተገቢ ከመሆኑም በላይ የሚሳካበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለቀጣናው ሰላምና ልማት ያላትን ታሪካዊ ሚና ያገናዘበ ነው ይላሉ።
በመሆኑም ለኢትዮጵያና ለቀጣናው ዘላቂ ጥቅም ሲባል የባህር በር ማግኘታችን አየቀሬ ነው ብለዋል።
ሌሎች ሀገራትም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያን ጥያቄ በአግባቡ ሊመልሱና በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።