በህዳሴ ግድብ እና በሌሎችም የሀገሪቷ አካባቢዎች ዓሳ የማምረት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴ ግድብ እና በሌሎችም የሀገሪቷ አካባቢዎች ዓሳ የማምረት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 19/2017(ኢዜአ)፦በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና በሌሎችም የሀገሪቷ አካባቢዎች ዓሳ የማምረት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፤ በተለይም የዓሳ ምርት ልማትና ተያያዥ የልማት ስራዎችን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ለዓሳ ምርት ልማት ሰፊ ሃብትና ምቹ ሁኔታ ቢኖርም ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን አስታውሰዋል።
በሀገሪቷ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ግን በአጠቃላይ በግብርና ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት በሀገሪቷ ጥራትና ብዛት ያላቸውን የዓሳ ምርቶች ማምረት የሚያስችላትን አቅም ለማሳደግ ፖሊሲዎችን ስትራቴጂዎችን እንዲሁም አቅጣጫዎችን በማውጣት ወደ ተግባር ገብቶ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም በህዳሴ ግድብ እና በሌሎችም የሀገሪቷ አካባቢዎች ዓሳ የማምረት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን የዓሳ ጫጩቶችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማሰራጨት አቅዶ በስፋት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም 4 ነጥብ 5 ሚሊየን የዓሳ ጫጩቶች ማሰራጨቱን ጠቅሰው፥በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዓሳ ልማት ዙሪያ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ በስፋት የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከሁለት ሳምንት በፊት 56 ቶን ዓሳ ማምረት ተችሏል ብለዋል።
በሀገሪቷ ዓሳ በብዛት ማምረት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም መኖሩን የገለጹት ሚኒስትር ዴታው፥ ለዚህ የሚመች መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው ብለዋለ።
በዘርፉ ልማት ለሚሰማሩ ሁሉ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የዘርፉን ልማት ይበልጥ ለማጠናከርና ውጤታማ ለማድረግ ከመንግስት ጥረትም ባለፈ የባለሃብቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።