አደጋን የመከላከል አቅምን ለማሳደግ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን የማሳተፍና የመመልመል ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
አደጋን የመከላከል አቅምን ለማሳደግ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን የማሳተፍና የመመልመል ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ አደጋን የመከላከል አቅምን ለማሳደግ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን የማሳተፍና የመመልመል ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ 174 ቋሚ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አደጋን ቀድሞ በመከላከል እና መቆጣጠር ላይ ስልጠና ሰጥቶ በዛሬው እለት አስመርቋል።
በኮሚሽኑ የማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር አለማየው ጦፉ በዚሁ ውቅት እንዳሉት፤ አደጋን የመከላከል አቅምን ለማሳደግ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን የማሳተፍና የመመልመል ስራው ይቀጥላል።
በከተማው እየጨመረ ከመጣው ህዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አደጋዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው ኮሚሽኑ ካለው የሰው ኃይል በተጨማሪ የበጎ ፍቃደኞች ሚና አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ከከተማ አስተዳደሩ ክፍለ ከተሞች በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በመመልመል ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማ አስተዳደሩ ቋሚ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አሰልጥኖ ማስመረቁን ገልጸዋል።
ወጣቶቹ ከአደጋ መቆጣጠርና መከላከል ጋር በተያያዘ በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች አሰልጥኖ በበጎ ፍቃደኝነት ማሰማራቱ የሚከሰቱ አደጋዎችን ፈጥኖ ለመቆጣጠር ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ከስልጠናው በቂ እውቅትና ክህሎት በማግኘት ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና እንዲወጡ ብሎም መልሶ በማቋቋም ረገድ ስልጠናው ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣቶቹ የተለያዩ ስራዎችን ከነባር ሰራተኞች ጋር በመቀናጀት ወደ ስራ እንደሚገቡ ገልጸው፤ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን ቤት ለቤት ጭምር እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።
የማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይም መሰል ስልጠናዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰጡ ነው የገለጹት።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ሰልጣኝ ወጣቶች መካከል ወጣት አንዱአለም አዳነ እና ራሄል ገዛህኝ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ውስጥ የሚከሰተውን አደጋ ቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ስልጠናው ትልቅ አቅም እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቀደም ሲል በርካታ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደነበር የገለጹት ወጣቶቹ በወሰዱት ስልጠና መሰረት ለህብረተሰቡ ስለ አደጋ መከላከል ግንዛቤ በመፍጠር የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።