ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ውጤቶች የገበያ ትስስር አቅምን እንዲያሳድጉ ልዩ ድጋፍ ይደረጋል

መቀሌ፤ ታህሳስ 18/ 2017 (ኢዜአ)፡-የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለትግራይ ክልል የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ውጤቶች የገበያ ትስስር በመፍጠር አቅማቸውን  እንዲያጎለብቱት ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ።

አገር አቀፍ አውደ ርዕይና ባዛር ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተከፍቷል። 

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዓውደ ርዕዩና ባዛሩ ላይ የቀረቡት የቴክኖሎጂ የምርት ውጤቶች ችግር የሚፈቱ በመሆናቸው በስፋት በማባዛት ወደ ተጠቃሚዎች መቅረብ ያለባቸው ናቸው። 

አገር አቀፍ ዓውደ ርዕዩና ባዛሩ በመቀሌ ከተማ መከፈቱ አምራቾች እና ስራ ፈጣሪዎች አቅማቸውን ፈትሸው ራሳቸውን እንዲያሳድጉ ከማድረግ ባለፈ ማህበራዊ ትስስሩ እንዲጠናከር ያደርጋል ብለዋል። 

የዘርፉ ውጤቶች በቀጣይ በሌሎች ክልሎችና ከተሞች በሚዘጋጁ ሀገር አቀፍ አውደ ርዕይና ባዛር ላይ እንዲቀርቡ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ በዚህም የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ሚኒስቴሩ ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል። 


 

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቴክኒክ፣ ሙያ፣ ትምህርት፣ ስልጠናና የስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ሀጎስ እንደገለጹት፤ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በክልሉ እየታየ ያለውን የስራአጥ ቁጥር በመቀነስና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው።

ዓውደ ርዕዩና ባዛሩ መከፈቱ የህዝቡን ስነ ልቦና ወደ ስራና አምራችነት እንዲያተኩር ይረዳዋል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የመቀሌ ቅርንጫፍም በአውደ ርዕዩና ባዛሩ ላይ ምግብ ነክ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ አቅርቧል። 

ከአዲስ አበባ የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎችን ይዘው በአውደ ርዕዩና ባዛሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ዳዊት አዳነ አውደ ርዕዩ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ምርታቸውን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቅማቸው ተናግረዋል።

አውደ ርዕዩና ባዛሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም