የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የግብዓት ተደራሽነትን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የግብዓት ተደራሽነትን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2017(ኢዜአ)፡- የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የግብዓት ተደራሽነትን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከሌሎች የምርምር ተቋማት ጋር በመሆን ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የዲጂታል የአፈር ማዳበሪያ መተግበሪያ ለመጠቀም የሚረዳ ምክረ ሀሳብ የማስተዋወቅ ሥራ ተካሂዷል።
ዲጂታል የአፈር ማዳበሪያ መተግበሪያውን የማልማት ሥራ ላለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና በተለያዩ የምርምር ተቋማት ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል።
መተግበሪያውን የምርምር ተቋማት፣ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እና የግብርና ጽህፈት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ሲተገብሩት የቆዩ ሲሆን ውጤታማ ነው ተብሏል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን(ዶ/ር) እንዳሉት የአፈር ማዳበሪያን በተቀናጀ ሁኔታ በዲጂታል መንገድ ተደራሽ ማድረግ ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ ወሳኝ ነው።
የተለያዩ የግብርና ምርምር ውጤቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።
እስከ አሁን የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ምክረ ሀሳቦች በአካል አርሶ አደሩን በማስገንዘብ፣ የተለያዩ ሕትመቶችንና መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ተደራሽ ሲሆኑ እንደነበር አስታውሰዋል።
አዲስ የለማው የተቀናጀ የዲጂታል የአፈር ማዳበሪያ መተግበሪያ የማዳበሪያ መጠን፣ አይነትና አጠቃቀምን በአንድ ማዕከል በቀላሉ ማሳወቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ ዘመናዊ አሰራሮችን እየዘረጋ ነው ያሉት ዶክተር መለሰ፥ የምግብና ስርዓተ ምግብን ማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎችም ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ገለቲ(ዶ/ር) በበኩላቸው መተግበሪያው ለአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ውጤታማነት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ከአንድ ማዕከል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በመጠንና በአይነት ተደራሽ ማድረግ እንደሚያግዝ ጠቅሰው፥ መተግበሪያውን የበለጠ ማስተዋወቅ የሚያስችሉ ስራዎች በቀጣይ እንደሚከናወኑ አንስተዋል።
ከአጋር ምርምር ተቋማት መካከል ከዓለም አቀፍ ሰብል ኢንስቲትዩት የመጡት ግዛው ደስታ(ዶ/ር)፥ በሞባይል መተግበሪያ፣ በድምጽ፣ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት፣ በቴሌግራም እና በሌሎች ዘዴዎች ለአርሶ አደሩ መረጃ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ነው የተሰራው ብለዋል።
ይህም ለግብርና ልማት ስኬት የሚያግዝ ሲሆን የአርሶ አደሩን ገንዘብ እና ጊዜ በመቆጠብ ረገድም ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል።