የቻይና እና የኢትዮጵያን በሁኔታዎች የማይቀያየር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና እና የኢትዮጵያን በሁኔታዎች የማይቀያየር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ18/2017(ኢዜአ)፦በተለያዩ የትብብር መስኮች የተመሰረተውን የቻይናና የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ አጋርነት ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ ገለጹ።
አምባሳደር ቼን ሃይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሁለቱ አገራት ለበርካታ ጊዜያት የቆየ ጠንካራ አጋርነት አላቸው ብለዋል።
አሁን ላይ ይህ ትብብር በሁኔታዎች የማይቀያየር ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂክ አጋርነት ላይ መድረሱን ጠቅሰዋል።
ሁለቱ አገራት ይህንን አጋርነት ይበልጥ በማጠናከር ከሁለትዮሽ በዘለለ በደቡባዊ የዓለም ክፍል የሚጫወቱትን ሚና ሊያጎለብቱ ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ስትራቴጂካዊ ሚና ያላት አገር መሆኗን ጠቅሰው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በቀጣናውም ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ጉዳዮችም በጋራ ተባብራ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያና ቻይና እንደ ብሪክስ አባል አጋርነታቸው ትብብራቸውን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ መሰማራታቸውን ገልጸው ይህንንም ይበልጥ ለማስፋት ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
በቅርቡ በቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ ከተካሄደው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ጉባኤ በኋላ በርካታ የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ወደ ኢትዮጵያም በብዛት እየመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ ዘርፎች የንግድ ትስስራቸውን ለማጠናከር የሚያስችል አቅም በሁሉቱም ወገኖች መኖሩን አንስተው ለዚህም የጋራ ጥረቶችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።