በክልሉ የሚከሰት ሰደድ እሳትን ለመከላከል የደን ጥበቃ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚከሰት ሰደድ እሳትን ለመከላከል የደን ጥበቃ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል
አሶሳ፤ ታህሳስ 18/2017(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የደን ሀብትን ከሰደድ እሳት ለመጠበቅ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የአካባቢ፣ ደን ሀብት ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ኃላፊ አቶ ሉቅማን አብዱልቃድር በሰጡት መግለጫ በክልሉ የደን ሀብት ውድመትን ለመከላከል በየወረዳው የደን ጥበቃ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።
በክልሉ ለደን ውድመት ዋነኛው መንስኤ የሰደድ እሳት መሆኑን የገለፁት ኃላፊው የእርሻ ማሳን ለማስፋት፣ የማዕድን ቁፋሮ እና አደንን ምክንያት በማድረግ የእሳት አደጋው እንደሚከሰት ተናግረዋል።
የሰደድ እሳት ከብዝሃ ህይወት ውድመት በተጨማሪ ለአየር ብክለት መንስኤ እንደሚሆንም ኃላፊው ጠቁመዋል።
የደን ሀብት መመናመን የአፈር መከላትን፣ የበረሃማነት መስፋፋትን እና የመሬት መራቆትን ስለሚያስከትል ህብረተሰቡ በደን ጥበቃ ዙሪያ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
ወቅቱ የሰደድ እሳት የሚከሰትበት በመሆኑ ህብረተሰቡ የሰደድ እሳት መከላከያ መስመር በመስራት አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎች ህብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ደንን በመጠበቅ ከ "ጥብቅ ደን" የእጣን ሙጫ ምርት እያገኘ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሉቅማን ይህም ከምርቱ በተጨማሪ የአካባቢው ስነ-ምህዳር እንዲመለስ አግዟል ብለዋል።
ባለስልጣኑ በክልሉ የሚገኘውን የደን ሽፋን ለማሳደግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ጥበቃ ስራ እያከናወነ እንደሆነም አክለዋል።
በክልሉ የደን ሽፋን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከፌዴራል መንግስት ጋር ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም አቶ ሉቅማን በመግለጫቸው አንስተዋል።