ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና እና የስኬት ተምሳሌት መሆን የሚያስችላትን ስራ እያከናወነች ነው -እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና እና የስኬት ተምሳሌት መሆን የሚያስችላትን ስራ እያከናወነች ነው -እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 18/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና እና የስኬት ተምሳሌት መሆን የሚያስችላትን ስራ እያከናወነች እንደምትገኝ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ”ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው፥ የለውጡ ዓመታት በተለያዩ መስኮች በተደረጉ ሪፎርሞች በርካታ ስኬቶች መመዘገባቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ሚና ሚዛናዊ እንዲሆን ማድረጉን አመልክተዋል።
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ የግሉ ዘርፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ እንደሚሆን መመላከቱን ተናግረዋል።
በሪፎርሙ ባንኮች በየዓመቱ ከሚሰጡት ብድር 70 በመቶ ገደማ የሚሆነው ለግሉ ዘርፍ እየሰጡ እንደሚገኝም ገልጸው፥ ይህም ለኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት መሰረት የጣለ መሆኑን አመልክተዋል።
ከባለፉት ስህተቶች በመማር በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ጥገኛ የነበረውን ኢኮኖሚ የባለ ብዝሃ ወገን የእድገት ምሰሶዎች እንዲኖሩት መደረጉን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት።
በግብርና፣ቱሪዝም፣ማኑፋክቸሪንግ፣ማዕድን፣ቱሪዝም እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ የተከናወኑ ሰፊ ስራዎች ፍሬ እያፈሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በግብርናው መስክ ምርታማነትን ለማሳደግ በተወሰዱ እርምጃዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቁጥር አንድ የስንዴ አምራች መሆን ችላለች ብለዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያለውን የምርታማነት አቅም በማሳደግ ረገድ ስኬታማ ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
በማዕድን ዘርፍ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት በተከናወኑ ስራዎች ባህላዊ የማዕድን አወጣጥ ዘዴን በመቀየር እና በዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የቱሪዝም እምቅ አቅምን ለመጠቀም በተከናወኑ ስራዎች የቱሪስት መዳረሻዎች በስፋት መልማታቸውን አመልክተዋል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የቱሪዝም እና የዓለም አቀፍ ሁነቶች መዳረሻ መሆን መቻሏን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ዲጂታላይዜሽን ግብ ለማሳካት በተከናወኑ ስራዎች በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች እየተደረገ ያለው ግብይት አሁን ላይ 9 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ብር መድረሱንና ከዓመታት በፊት ከነበረው 45 ቢሊዮን ብር አኳያ ከፍተኛ እምርታ ማሳየቱን ጠቁመዋል።
የዲጂታል ቁጠባና ብድርን ጨምሮ የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶች ተደራሽነት እና ተጠቃሚነት ማደጉንም ገልጸዋል።
በለውጡ ዓመታት አጠቃላይ አገራዊ ጥቅል ምርት እና የዜጎች ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ በሁለት እጥፍ ማደጉንና የግብር ገቢ መጠንም በሶስት እጥፍ መጨመሩን ጠቁመዋል።
በኢኮኖሚ ሪፎርሙ የኢትዮጵያን የውጭ እዳ ከአገራዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) አንጻር ያለው ምጣኔ ወደ 13 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያብራሩት።
በእዳ ውስጥ የነበሩ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ላይ የተወሰዱ የአሰራር ማሻሻያዎች ድርጅቶቹን ወደ ትርፋማነት እንዳሸጋገራቸው አመልክተዋል።
በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝግባቸውንና ኢኮኖሚው በትክክለኛ ጎዳና ላይ እንደሚገኝ አመላካች ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ ያላቸው መስተጋብር ላይ ያላቸው እሳቤ በሁሉም መስኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን አብራርተዋል።
መንግስት ከባለፉት ስርዓቶች እዳን ቢረከብም ለመጪው ትውልድ ሀብት እና ምንዳን ለማስተላለፍ አበክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለውጡን ማሳለጥ የሚያስችል የተቋማት አቅም ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና እና የስኬት ተምሳሌት መሆን የሚያስችላትን ስራ እያከናወነች መሆኗን ገልጸዋል።