ከሕዳሴ ግድብ እየመነጨ ያለው ኃይል የተለያዩ አካባቢዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እያደረገ ነው - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
ከሕዳሴ ግድብ እየመነጨ ያለው ኃይል የተለያዩ አካባቢዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እያደረገ ነው - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 18/2017 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሆለታ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እየመነጨ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በማከፋፈል የተለያዩ አካባቢዎችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ተቋሙ አስታወቀ።
የጣቢያው ኃላፊ አቶ ጥላሁን አዘዘው እንዳሉት፥ የማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 750 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሰባት ትራንስፎርመሮች አሉት፡፡
ጣቢያው በአሁኑ ወቅት ከሕዳሴ ግድብ በአራት ተርባይን እየመነጨ ያለውን 1500 ሜጋ ዋት ኃይል ከዴዴሳ ማከፋፈያ ጣቢያ ተቀብሎ ወደ ተለያዩ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እያሰራጨና ከግሪዱ ጋር እያገናኘ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ከደዴሳ በባለ 500 ኪሎ ቮልት አራት መስመሮች ኃይል ተቀብሎ በ400 ኪሎ ቮልት በጥምር መስመር ለሱሉልታ፣ ለሰበታና ለገላን ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ጣቢያው ሕዳሴ ግድብ ቀሪ ተርባይኖች ወደ ሥራ ሲገቡ የመነጨውን ኃይል በሙሉ ተቀብሎ በአግባቡ ለማከፋፈል ዝግጁ ነው ብለዋል።
ጣቢያው የአገር ውስጥ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለውጭ አገራት ኃይል ለማቅረብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት አቶ ጥላሁን።
ጣቢያው ብሔራዊ የኃይል ቋትን በማረጋጋት በኩል ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ታሳቢ ያደረገ የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ተርባይኖች 5 ሺ 150 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።