የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር ሊጀምር መሆኑን ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር ሊጀምር መሆኑን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 17 /2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በሁለት የትምህርት ዓይነቶች የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሀ ግብር ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው በ2018 የትምህርት ዘመን በደህንነት ጥናቶች እና በስትራቴጂ ደህንነት አመራርነት የትምህርት ዓይነቶች በሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር ለማስጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ የ78 ዓመት አንጋፋ ተቋም የሆነው ዩኒቨርሲቲው ከሰርተፍኬት ጀምሮ ዛሬ በሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር ለመስጠት መብቃቱ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ታላቅ ኩራት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለውጡን ተከትሎ ስትራቴጂክ አመራሩ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የጥናትና የምርምር ተቋም ሆኖ ከኢትዮጵያ ፖሊስ አልፎ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት የትምህርት ዕድል እየሰጠ የፖሊስ መኮንኖችን ማብቃቱን የፌደራል ፖሊሲ መረጃ ያመለክታል።
የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ተሻለ ሚቆሬ በበኩላቸው የነገውን ትውልድ ማነፅ የሚችል የትምህርት ተቋም በመገንባት፣ የኢትዮጵያ ፖሊስን በተማረና በሰለጠነ የሰው ሀይል በመገንባት ክፍተቶችን በመሙላት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች የምርምርና የትምህርት ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆንም ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።