ለቢሾፍቱ ከተማ ለውጥና እድገት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስተዋፅኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 17 / 2017(ኢዜአ)፦ለቢሾፍቱ ከተማ ለውጥና እድገት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስተዋፅኦ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

ለቢሾፍቱ ኮሪደር ልማት ተቋሙ ከባለሀብቶች እና የልማት አጋር ግለሰቦች ጋር በመተባበር ያስገነባቸውን የልማት ፕሮጀክቶች ከከተማው ለተውጣጡ የባለሀብቶች ቡድን አስጎብኝተዋል።

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥የቢሾፍቱ ከተማ እና አየር ኃይል የረዥም ዘመናት ቁርኝት ያላቸው ናቸው።

በጊዜ ሂደት ሁሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለከተማው ዕድገት የራሱን በጎ አሻራ ማስቀመጡንም ተናግረዋል።

ከተማዋን በሀገሪቱ ቁጥር አንድ የቱሪስት መዳረሻ ስማርት ሲቲ ለማድረግ በተጀመረው የኮሪደር ልማት ላይ አየር ኃይል ንቁ ተሳታፊ መሆኑንም አስታውቀዋል።

አያይዘውም፥ ከከተማ አስተዳድሩ ጋር በልማት ፤ በፀጥታ እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብሮ እንደሚሰራና የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው፥በከተማው የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወኑ ነው።

የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ጨምሮ መላው የከተማው ማህበረሰብ እና ባለሀብቶች እያደረጉት ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማመስገናቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም