ቀጥታ፡

በፀረ-ተባይ ኬሚካሎች ስርጭትና አጠቃቀም ጉድለቶች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው-ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 17/2017(ኢዜአ)፦ በፀረ-ተባይ ኬሚካሎች ስርጭትና አጠቃቀም ጉድለቶች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

የግብርና ሚኒስቴር የፀረ-ተባይ አስተዳደር፣ አያያዝና አጠቃቀምን በሚመለከት ከክልል ተጠሪ ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ግብርና የዜጎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በሻገር የሀገርን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።


 

ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት ዘርፉን ለማሳደግና የግብርና ምርት ውጤታማነትን ለማጎልበት በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የጸረ-ተባይ ኬሚካሎች ሰብልን ከጉዳት ለመከላከል ወሳኝ ሚና ቢኖራቸውም በአጠቃቀም ላይ ያለው ክፍተት ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው አንስተዋል።

ኬሚካሎች ከአካባቢና የአየር ሁኔታ ጋር ያላቸውን ተስማሚነት አለመፈተሽ፣ የኬሚካል ጥራትና ስርጭት መጓደል ችግሩን አሳሳቢ እያደረገው ነው ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለተጠቃሚው በቀጥታ እንዲደርሱ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ህገ ወጥ የጸረ ተባይ ኬሚካሎች ስርጭትና አጠቃቀም ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ደንብና መመሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የፀረ-ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ክፍተትን ለማረም ደግሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ባለድርሻ አካላትም ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች የግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የቅንጅት ሥራ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የጸረ ተባይ ቁጥጥር ባለሙያ የዓለም ብርሃን መርጊያ በክልሉ የጸረ ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ክፍተትን ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን የግብርና አስተባባሪ መለሰ ልይህ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመን ወጥነት ያለው አሰራር ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም