ቀጥታ፡

ምርምር ማዕከሉ የአየር ንብረት ተፅዕኖን የሚቋቋሙ የቆላ ስንዴ ዝርያዎችን ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ነው

አዳማ፤ ታኅሣሥ 17/2017 (ኢዜአ)፦ የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የአየር ንብረት ተፅዕኖን የሚቋቋሙ የቆላ ስንዴ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።

ማዕከሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በግብርና መካናይዜሽን ቴክኖሎጂና በቆላ ስንዴ ምርምር ላይ ያከናወናቸውን ስራዎች በአዳማ ከተማ ገምግሟል ።


 

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ዶክተር ቶሎሳ ደበሌ እንደገለፁት የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የቆላ ስንዴን ጨምሮ በጥጥ፣ በቆላ ጥራጥሬና በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ ምርምር እያካሄደ ነው ።

ማዕከሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት 'አዳፕት' በተሰኘ ፕሮጄክት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የሚቋቋም የቆላ ስንዴ በምርምር ማግኘቱን ጠቁመዋል።

በተለይ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ለቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች የአየር ጠባይ ተስማሚ የሆኑ የቆላ ስንዴ ዝርያዎችን ለአሚባራ፣ አዋሽ ፈንታሌ፣ ቦሰትና አዳማ ወረዳዎች ለአርሶና አርብቶ አደሮች ተደራሽ ማድረጉን ተናግረዋል ።

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ዓለማየሁ በበኩላቸው ማዕከሉ ለአካባቢው አርሶና አርብቶ አደሮች በአየር ሁኔታና የውሃ መጠን እንዲሁም በመስኖ ውሃ አጠቃቀም ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በግብርና መካናይዜሽን ምርምር ስራዎች የእርሻ፣ የመከስከሻ፣ ማለስለሻ፣ የመዝሪያና ማጨጃ መሳሪያዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረጉን ገልጸዋል።

በአዳፕት ምርምር ፕሮጄክት "አሊ ሚራህ" የተሰኘ የዳቦ ስንዴና "ደሃፕ" የተሰኘ የማካሮኒ የቆላ ስንዴ ዝርያ በምርምር ማውጣቱን አመልክተዋል።

ዘላቂ የሥነ ሕይወት ስርዓትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ ፕሮጄክት መሆኑን የገለጹት ደግሞ አዳፕት የዳቦ ስንዴ ምርጥ ዘር ማሻሻያ ፕሮጄክት አስተባባሪ ዶክተር ቶሎሳ ዘለቀ ናቸው።

በተለይ በዝቅተኛ ቆላ ቦታዎች የስንዴ ምርትና ምርታማነትን የሚያጎለብቱ የስንዴ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማውጣትና የማስተዋወቅ እንዲሁም የማስፋፋት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል ።

የስንዴ ዝርያና የእርሻ መሳሪያዎች በምርምር በማውጣት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው በዚህም የቆላ መስኖ ስንዴ ልማትና ምርታማነት እንዲጨምር አስተዋፆ መደረጉን ጠቅሰዋል።

"በአፋርና ኦሮሚያ ክልሎች በሰባት ወረዳዎች ቴክኖሎጂውን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ በማድረግ ምርታማነት እንዲጎለብት ተደርጓል" ሲሉም አክለዋል።

በዚህም ከ4 ሺህ 300 በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች በፕሮጀክቱ የምርምር ውጤቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም