የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ተደርጓል-የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ተደርጓል-የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 17/2017(ኢዜአ)፦በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ለማስቻል የቅድመ ዝግጅቱን ተግባራት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
ከበአሉ ጋር ተያይዞ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ረምዚ ሱልጣን እንዳሉት፥ በዓሉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር ለማስቻል ለሁሉም ፈፃሚ አመራር እና አባላት እንዲሁም አጋዥ ተቋማት የበአሉን አከባበር የተመለከተ የፀጥታ እቅድ ወጥቶ በቂ ግንዛቤ ተጨብጧል።
የበአሉ አከባበር ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊ የሰው ኃይል ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም፥ ከበአሉ ጋር ተያይዞ ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶች እና ነዋሪው አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ወድያውኑ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የትራፊክ አደጋዎች እንዳይደርሱ ለመከላከል መላ አሽከርካሪዎች በትእግስት እና የመንገድ አጠቃቀም ህግና ስርአትን ባከበረ መልኩ ማሽከርከር ይገባልም ብለዋል።
ኮሚሽነሩ ባስተላለፉት መልዕክትም፥ ሰላም ወዳዱ የክልሉ ህዝብ እንደ ወትሮው ሁሉ አሁንም ከፖሊስና ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር እንዲተባበር ጥሪ ማቅርባቸውን ከሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን የተገኘ መረጀያመለክታል።