የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና የተደራሽነት ክፍተትን ለማስተካከል ይረዳል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2017(ኢዜአ)፡- የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና የተደራሽነት ክፍተትን ለማስተካከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሳስ 8 ቀን 2017 ዓ.ም የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅደውን የባንክ ሥራ አዋጅ ማጽደቁ ይታወቃል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግርን ለመፍታትና በአነስተኛ ወለድ ብድር ለማግኘት ያግዛል፡፡

እንዲሁም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በተለምዶ ሲሠራበት የነበረውን የባንክ ስራ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል።

ገበያው ክፍት መደረጉን ተከትሎ በሀገር ውስጥ ያሉት ባንኮች ከውጭ ከሚመጡ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የገቢ አድማሳቸውን ማስፋት እንዳለባቸውም እንዲሁ።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የማክሮ ፖሊሲ ክፍል አስተባባሪ ተወልደ ግርማ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት የዓለም ባንክ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ የባንክ ደብተር ያላቸው ዜጎች 60 በመቶ ናቸው።

ይህንን ቁጥር ለማሳደግና በአለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው መስፈርት ልክ የባንክ ተገልጋዮችን ጥምርታ ለማስተካከል በየአመቱ ከ500 በላይ ቅርንጫፎችን መክፈት ያስፈልጋል ብለዋል።

የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር እንዲገቡ መፈቀዱ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና የተደራሽነት ክፍተትን ለማስተካከል እንደሚረዳም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተዋናያኑን በበቂ ሁኔታ የሚያሳትፍ ሰፊ አቅም እንዳለ ነው ዶክተር ተወልደ የተናገሩት፡፡

የውጭ ባንኮች በዘርፉ እንዲሰማሩ መፈቀዱ ውድድር እንዲኖር ከማስቻሉ ባለፈ የሀገር ውስጥ ባንኮች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንዲዘጋጁ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

የውጪ ባንኮች ልምዳቸውንና ቴክኖሎጂዎችን ይዘው ስለሚመጡ ዘርፉን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ ተናግረዋል።

ለተገልጋዩ ተጨማሪ የብድር አገልግሎት ለማቅረብና የወጪ ንግዱን ለማሳደግ እድል እንደሚኖረውም ነው ያነሱት።

የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ከሚገቡት ጋር ተወዳዳሪ ሆነው ለመቀጠልም የገቢ ምንጫቸውን ከወለድ ጥገኝነት በማውጣት ሌሎች ዘርፎችን ማየት እንደሚገባቸው ነው ምክረ ሐሳብ ያቀረቡት።

ከዚህ ውስጥም ኢንቨስትመንት እና ሐብት አስተዳደርን ጨምሮ በካፒታል ገበያው በስፋት መሳተፍን እንደ አማራጭ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ነው ያሉት።

ዲጂታል ቴክኖሎጂን ይበልጥ ማጠናከር፣ አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ አጢነው መጓዝ ከቻሉ የሀገር ውስጥ ባንኮች ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም