የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 60 በመቶ ማድረስ ተችሏል - አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 60 በመቶ ማድረስ ተችሏል - አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2017(ኢዜአ)፡- በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ወደ 60 በመቶ ማሳደግ መቻሉን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
ከአምስቱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ምሰሶዎች መካከል የኢንዱስትሪው ዘርፍ አንዱ ነው፡፡
በለውጡ አመታት የአምራች ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ድርሻ ለማሳደግ እና በሥራ ላይ ባለው ስትራቴጂና ፖሊሲ አቅጣጫዎች ያልተፈቱ ክፍተቶችን መሙላት የሚያስችል ፖሊሲ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ፖሊሲው የዘርፉን የመልማት አቅምና መልካም አጋጣሚዎች አሟጦ ለመጠቀም እና ከዘርፉ ተለዋዋጭ ባህሪያት ጋር የሚመጡ የምርት ስርዓት ሁኔታዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ነው።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ባለፉት የለውጥ አመታት የአምራች ኢንዱስትሪውን ተግዳሮቶች ለመፍታት እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኤክስፖርት ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውስጥ ገበያ ማምረት እንዲችሉ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ተወዳዳሪነታቸው እንዲያድግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አንስተዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ላይ ማሻሻያ በመደረጉ፤ ከለውጡ በፊት ወደ 46 በመቶ ወርዶ የነበረው የማምረት አቅም አሁን ላይ ወደ 60 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት።
በዚህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከፍ ማለቱን ተከትሎ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ የራሱን አዎንታዊ ሚና እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከለውጡ በፊት 30 በመቶ የነበረው የአምራች ኢንዱስትሪው የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ አሁን ላይ ወደ 40 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው ድርሻ እጅግ ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑን አስረድተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪው የውጭ ባለሀብቶች ፍሰትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው ወደ ማምረት የሚገቡ የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥርም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በአመት በዘርፉ ለዜጎች የሚፈጠረው የስራ እድል የመፍጠር አቅምም 156 ሺህ በላይ መድረሱን አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።