በለውጡ ዓመታት የመንግሥትን አገልግሎት የሚያዘምኑና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈቱ ሪፎርሞች ተደርገዋል - ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በለውጡ ዓመታት የመንግሥትን አገልግሎት የሚያዘምኑና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈቱ ሪፎርሞች ተደርገዋል - ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2017(ኢዜአ)፡- የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፣ በለውጡ ዓመታት በአገልግሎት አሰጣጥና በመልካም አስተዳደር እና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አካታች በሆነ መልኩ የተመሰረተው ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም ረገድ የሚታዩና የሚጨበጡ ውጤቶችን አስመዝግቧል ብለዋል።
ፓርቲው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና በነፃነት የማስተዳደር መብት ተግባራዊ እንዲሆን በመስራቱ ክልሎች በዚሁ ልክ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዳርና የመሃል በሚል ሁሉንም ያላሳተፈና አግላይነት የሚስተዋልበት አሰራር እንደነበር አስታውሰዋል።
በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የተመሰረተው ብልፅግና ፓርቲ አካታችና ሁሉንም አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት መተግበሩን ገልጸዋል።
በዚህም ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል እንዲሳተፉና የመወሰን ስልጣን እንዲኖራቸው ዕድል በመፍጠር በሁሉም ዘርፎች ስኬት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
በለውጡ ሂደት የተገኙ ውጤቶችን በላቀ መልኩ ለማስቀጠል ችግሮች እየተገመገሙና እየተፈቱ ስኬታማ የሆኑ የልማት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።
አመራሩ ለዜጎች ሥነ ምግባር በተላበሰ መንገድ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮች እስከታችኛው መዋቅር ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም ነው ርዕሰ መስተዳድሯ የገለጹት።
ከሥነ ምግባር ውጪ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አመራሮችን በግምገማ በማጥራት የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።