ቀጥታ፡

አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል የአንካራው ስምምነት ልምድ የሚወሰድበት ነው - ምሁራን

ሐረር፤ ታህሳስ 17/2017(ኢዜአ)፡- በተለያዩ ጊዜያት ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት መፍታት እንደሚቻል የአንካራው ስምምነት ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ኢዜአ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።

የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ ቀጣናዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን በትብብር መፍታት የምትችል መሆኗን በተግባር ያንጸባረቀ እንደሆነም ገልጸዋል።

በቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አቀራራቢነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሀገራቱ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ስምምነቱ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ እውን ማድረግ የሚያስችልና ለቀጣናው ሰላምና የጋራ ልማት ወሳኝ ስለመሆኑም በወቅቱ ተገልጿል።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለምታነሳው የባህር በር ጥያቄ ሁነኛ ምላሽ የሚሰጥና ብሄራዊ ጥቅሟንም በዘላቂነት ማስጠበቅ የሚያስችል መሀኑን ነው ምሁራኑ የተናገሩት።

ስምምነቱ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ተገቢነት በብዙዎች ዘንድ እንዲታመን ያደረገ እና ዓለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆን ያስቻለ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአንካራው ስምምነት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ የትብብር ግንኙነት መፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት ግጭቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ እንደሆነም እንዲሁ።

በጉዳዩ ላይ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል መምህር አብዮት አስማማው እና በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር አቶ ሞገስ አበበ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

መምህር አብዮት አስማማው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቋንቋ፣ በባህል፣ በታሪክና በተፈጥሯዊ ስነ ምህዳር ትስስር ያላቸው ሀገራት ናቸው።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው ስምምነትም በቀጣናው ያሉትን እድሎች ለመጠቀምና ለማልማት ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ በአፍሪካ ህብረትና ኢጋድ የተሰጣትን ሃላፊነት በብቃት እንድትወጣ ከማድረግ ባለፈም ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም የሶማሊያን አለመረጋጋት ተከትሎ አልሻባብ የሚፈፅመውን የሽብር ጥቃት ለመከላከልና ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ትልቅ ስራ ለመስራት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

በቀጣናው ትላልቅ የኢንቨስትመንት ፍሰቶችን ማምጣት የሚያስችልና በተሻለ የእድገትና የልማት አካባቢ ምቹ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስነ ምህዳርን የሚፈጥር መሆኑንም አክለዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰፊ መሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ሀብቶቹን በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስምምነቱ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሞገስ አበበ በበኩላቸው የአንካራው ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዳይኖር የሚሹ ኃይሎችን ፍላጎት ያከሸፈና ኢትዮጵያ በሰላም የባህር በር የማግኘት ጽኑ ፍላጎቷን ያመላከተ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የውጪ ፖሊሲ ቀድሞውንም ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ጉርብትናና አብሮ የመልማት ጽኑ ፍላጎት ያላት መሆኗን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

አሁን ላይም ኢትዮጵያ እያቀረበች ያለው የባህር በር ጥያቄ በቀጣናው አብሮ የመልማትና የማደግ ጥያቄ እንጂ ሌላ ስጋት የሚፈጥር አለመሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በአንካራ ከሶማሊያ መንግስት ጋር ያደረገችው ስምምነት ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላም አብሮ የመልማትና የማደግ ፍላጎቷን ያመላከተ መሆኑን አስገንዝበዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም