ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር ማለፍ አልቻለም 

 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16 /2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ በሱዳን በደርሶ መልስ ውጤት ተሸንፎ ለውድድሩ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ በሊቢያ ቤንጋዚ ማርትያርስ ኦፍ ፌብሩዋሪ ስታዲየም ባደረገው የመልስ ጨዋታ በሱዳን 2 ለ 1 ተሸንፏል።

ሞሲ ካንቴ እና ሙሐመድ አብዱልራህማን የማሸነፊያ ግቦቹን ለሱዳን አስቆጥረዋል።

የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ብርሃኑ በቀለ ለኢትዮጵያ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ውጤቱን ተከትሎ ሱዳን በድምር ውጤት 4 ለ 1 በማሸነፍ ለቻን ውድድር ማለፏን አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን የማጣሪያ ጉዞ በመጨረሻው ዙር ማጣሪያ ተገቷል።

ስምንተኛው የቻን ውድድር ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም በኬንያ፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል።

በቻን ውድድር አዘጋጆቹን ጨምሮ 19 አገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም