የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቅረፍ በቅንጅት ይሰራል - ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ - ኢዜአ አማርኛ
የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቅረፍ በቅንጅት ይሰራል - ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2017(ኢዜአ)፡- የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን መቀነስ ለአወንታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቅንጅት ይሰራል ሲሉ የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ገለጹ፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በሀገራዊ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ፣ ዘገባና ማረጋገጫ ስርዓት ላይ ከሰባት ሴክተር ተቋማት ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምንቱን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የደን ልማት ከኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ተፈራርመዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በወቅቱ እንደገለጹት ሀገራችን በ2030 የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በ68 ነጥብ 8 በመቶ ለመቀነስ ቃል ገብታለች፡፡
ይህን ማሳካት የሚያስችል ቅንጅት መፍጠር ያስፈልገናል ብለዋል፡፡
ስምምነቱም የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን ለመቀነስ እንዲሁም በሀገራችን የተጀመሩ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
የሀገራችን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ልኬት፣ ዘገባ እና ማረጋገጫ ስራዎችን ማጠናከር እና በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱን ያደረጉ ተቋማት በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ስትራቴጂዎችን ለመተግበር በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን መቀነስ ለአወንታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በረኦ ሃሰን በበኩላቸው ስምምነቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሃሰን ሙሃመድ፤ ስምምነቱ በአየር ንብረት ምክንያት እንደሀገር የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለማስቀረት የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡
ስምምነቱ በዋናነት ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስርዓት እውን ማድረግ ያስችላል ያሉት ደግሞ የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ መሀመድራፊ አባራያ ናቸው።