አዋጁ የተራቆቱ አካባቢዎችን በዘላቂነት ለማልማት የሚደረገውን ጥረት በላቀ መልኩ የሚያግዝ ነው - የኢትዮጵያ ደን ልማት - ኢዜአ አማርኛ
አዋጁ የተራቆቱ አካባቢዎችን በዘላቂነት ለማልማት የሚደረገውን ጥረት በላቀ መልኩ የሚያግዝ ነው - የኢትዮጵያ ደን ልማት
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2017(ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር አዋጅ የተራቆቱ አካባቢዎችን በዘላቂነት ለማልማት የሚደረገውን ጥረት በላቀ መልኩ የሚያግዝ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትላንትናው እለት ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባ የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር አዋጅ አጽድቋል።
የአዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም፤ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል።
ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቅ ሙቀት አማቂ ጋዝ፣ የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት አለመጠበቅ፣ የአያያዝና ሌሎችም ምክንያቶች ለአየር ንብረት ለውጥ መዛባት አይነተኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ በተለይም ታዳጊ ሀገራት ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት ልማት አርአያነት ያለው ስራ እያከናወነች መሆኑን አንስተው በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች መታየታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎችን በዘላቂነት በማልማት በፍጥነት እንዲያገግሙ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ የዘርፉ ልማት ቀጣይነትና ስኬታማነት የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር አዋጅ መጽደቁ ልዩ ትርጉም አለው ነው ያሉት።
የተወሰደው እርምጃም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ለመከላከል ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የአዋጁ ተግባራዊ መሆን ኢትዮጵያ እያከናወነች ላለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ የአረንጓዴ ልማት ስኬትና የሙቀት አማቂ ጋዝን ለማስወገድ የላቀ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል።
በአዋጁ መሰረት መንግስት ከ0 ነጥብ 5 እስከ 1 በመቶ በየአመቱ ገንዘብ እንዲመድብ የሚያደረግ ይሆናል ብለዋል።